ሴት ልጆች በኢትዮጵያ ያለው ጦርነት እንዴት ህይወታቸው እና ትምህርታቸው ላይ ተጽእኖ እንዳመጣ ያካፍላሉ፡፡

Ruth Yitbarek  | 

ከአማራ ክልል የመጡ ሶስት ሴት ልጆች ስለ መፈናቀል፣ ስለ ጾታ ተኮር ጥቃት እና የስሜት መቃወስን ስለመቋቋም ይጽፋሉ፡፡

በህዳር 2013 ዓ.ም. በሰሜን ኢትዮጵያ፣ በኢትዮጵያ መንግስት እና የትግራይ ክልል ገዢ ፓርቲ በሆነው ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህውሓት) መካከል የሽምቅ ጦርነት ተጀመረ፡፡

እስከዛሬ፣ በመቶዎች እና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት አልፏል፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደግሞ ተፈናቅለው ነበር፡፡ በትግራይ እና በአጎራባች ክልሎች በሁለቱም ወገን፣ የትምህርት ቤት ህንጻዎችን እና ግቢዎችን እንደመዋጊያ ስፍራ እና ለተፈናቃዮች እንደመጠለያ ስለሚጠቀሙ፣ 2509 ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ነበር፡፡ ሪፖርቶች እንደሚገምቱት የቅርብ ጊዚው ግጭት እና የተፈጥሮ አደጋ በኢትዮጵያ ከ2.9 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ልጆች ከትምህርታቸው እንዲስተጓገሉ አስገድዷቸዋል፡፡

ከአማራ ክልል (አታዬ እና ደብረሲና) የመጡ ሶስት ኢትዮጵያዊ ሴት ልጆች ግጭቱ እንዴት ህይወታቸው እና ትምህርታቸው ላይ ተጽእኖ እንዳሳደረ ይጽፋሉ፡፡ ለመንግስታ ያሏቸውን ጥያቄዎች እና ከመሪዎች ምን አይነት ድጋፍ ማየት እንደሚፈልጉም ያካፍላሉ፡፡ እነዚህ ወጣት ሴቶች ካጋጠሟቸው አድሎዎች፣ የእኩልነት መጓደል እና ጥቃት ባሻገር ለወደፊት ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ሴት ልጆች የተሻለ ህይወትን ለመገንባት አስደናቂ ጥንካሬ እና ቁርጠኝነትን ያሳያሉ፡፡ 


ሳምራዊት ታዬ፣ 17፣ ደብረሲና

ሳምራዊት ከደብረሲና የ11ኛ ክፍል የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ናት፡፡ የእሷን ፈለግ ተከትለው ትምህርት ሊማሩ የሚያቅዱ ሶስት ታናናሽ ወንድም እና እህቶችም አሏት፡፡ ስታድግ ደግሞ ዶክተር መሆን ትፈልጋለች፡፡ 

ከጦርነቱ እና ከኮቪድ በፊት የተሻለ ትምህርት እና የመማሪያ አካባቢ ነበረን፡፡ በከተማ ትምህርት ቤቶች እንዳሉ ሴት ልጆች ላይሆን ይችላል ለእኛ ግን ለወደፊቱ ማለም እና የተሻለ ሰው ለመሆን መመኘታችን እና ለእኛም ለቤተሰቦቻችንም ትልቅ ነገር መወጠናችን በቂ ነበር፡፡ 

ጦርነቱ በተለይም ለሴት ልጆች እጅግ የሚያዘናጋ ነበር፡፡ በጦርነቱ ጊዜ … ካላያችሁት አይገባችሁም እንዴት ብዬ እንደምነግራችሁ አላውቅም፡፡ ብዙ ሴቶች ተደፍረው ነበር፤ ቤቶች እና ትምህርት ቤቶች ተቃጥለው ነበር፤ ብዙ ቤተሰቦች ልጆቻቸውን ወደትምህርት ቤት መላክ አይችሉም ነበር፡፡ አብዛኛዎቹ ጓደኞቻችን ጦርነቱን ተቀላቅለው ነበር፤ ብዙዎቹ ሴት ልጆች አሁን አግብተዋል፡፡ በዚህ ሁሉ ምክንያት ወደትምህርት ለመመለስ ምንም አይነት ተነሳሽነት አልነበረንም፡፡ አንድ ጥቅል የመማሪያ ደብተር ዋጋው 800 ብር ነው ስለዚህ ብዙ ቤተሰቦች የመግዛት አቅሙ የላቸውም፤ ተማሪዎቹ ደግሞ እነዲህ ብለው እራሳቸውን ይጠይቃሉ ” ምን ዋጋ አለው?“ እና “ደግሞስ ለየትኛው ህልም? ”፤ ብዙ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ያልተመለሱት ለዛ ነው፡፡ 

በደንብ ካሰባችሁት ጦርነቱ ያጠፋው ትምህርት ቤቶቻችንን ብቻ ሳይሆን ተስፋዎቻችንን እና ህልሞቻችንንም ጭምር ነበር፡፡ 

ልብ በሉ ስለዚህ ችግር ሁሉንም ነገር ስነግራችሁ በደብረሲና ያለው የእኔ ማህበረሰብ ከሌላው የቀለለ ተሞክሮ ነበረው፡፡ በቆቦ፣ በአታዬ እና በመሳሰሉት ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመት አያቅተኝም፡፡ እኔ የተወለድኩት ደሴ ነበር እዛ ብዙ ቤተሰቦች ነበሩኝ ብዙዎቹንም አጥቻለሁ፡፡ 

መንግስት እየተካሄደ ስላለው ነገር ሳያውቅ ቀርቶ አይመስለኝም፡፡ ብዙ ቤተሰቦች ሁሉንም ነገር አጥተዋል፡፡ ከዚህ ህይወት ልንወጣ የምንችልበት ብቸኛው መንገድ ትምህርት እንደሆነ አምናለሁ፡፡መንግስት ቤተሰቦች ተመልሰው እራሳቸውን እንዲያቋቋሙ፣ ልጆቻቸውን መልሰው ወደ ትምህርት ቤት መላክ እንዲችሉ እና ልጆቻቸው ወደትምህርት ቤት ለመሄድ ምክንያት እንዲኖራቸው እና ለወደፊት የሆነ ነገር ወይም የተሻለ ሰው ለመሆን እንዲያልሙ ለማገዝ የሆነ ነገር ማድረግ ቢችል ጥሩ ነው፡፡ 

ተማሪዎች ላሳለፉት ሁሉ ከባድ ጊዜ የእኔ ትምህርት ቤት የስነ ልቦና ድጋፍ አይሰጥም፡፡ ተማሪዎች ምንም ነገር እንዳልተከሰተ ተመልሰው ትምህርት ቤት እንዲገቡ መጠበቅ ከባድ ነው፡፡ የስነልቦና ድጋፍ ማግኘት ብንችል ጥሩ ይሆናል፡፡ ማንም ሰው በእርግጥ እኔ ደህና ነኝ ማለት አይችልም፡፡ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ እየተከሰተ ባለው ነገር መነካታችን አይቀርም፡፡ 


አይናለም ተምትሜ፣ 19፣ አታዬ

አይናለም ከአታዬ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነች፡፡ በሃይስኩሏ ከፍተኛ ውጤት ከሚያመጡ ተማሪዎች መካከል አንዷ ሰትሆን ከቤተሰቧ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ለመጨረሰ የመጀመሪያዋ ናት፡፡

ከጦርነቱ በፊት ትምህርት ቤት ደስ ይል ነበር፡፡ እንደ ሴት ልጅ ግን ብዙ ችግሮች ነበሩብን፣ ለእኛ መቼም ቀላል አልነበረም፤ ሆኖም ግን ደስ ይል ነበር፡፡ እንደ ሚኒ ሚዲያ፣ የሴቶች ክበብ እና ብዙ ሌሎች ከመደበኛ ትምህርት ውጪ እንቅስቃሴዎች ነበሩን፡፡ ምንም የሚያጠራጥር ነገር አልነበረም፡፡

ትክክለኛ ትምህርት የነበረን እስከ ዘጠነኛ ክፍል ብቻ እንደነበር በሙሉ እምነት መናገር እችላላሁ፡፡ ከዛ በኋላ ኮቪድ ተከሰተ አሁን ደግሞ ጦርነት፡፡ 

ስለኮቪድ ብዙ እናማርር ነበር፡፡ በእርግጥም ትምህርታችንን አስተጓጉሎብናል አብረውትም የመጡ ብዙ ችግሮች ነበሩ፡፡ አሁን ግን ጦርነቱን ካየሁ በኋላ ኮቪድን በአንጻሩ በጣም የተሻለ ያደርገዋል፡፡ ጦርነቱ ህልሞችህን እና ተስፋህን ያሳጣሃል ሰብአዊነትህንም እንድትጠራጠር ያደርግሃል፡፡ ከጦርነቱ በፊት ዶክተር መሆን ፈልገህ ከነበረ አሁን አነስተኛ የሱቅ ነጋዴ ወይም ተመሳሳይ ነገር መሆንን ትመኛለህ፡፡ ጦርነቱ ጓደኞችህን፣ ቤተሰቦችህን እና ለተሻለ ነገ ያለህን ተስፋ እንድታጣ ያደርግሃል፡፡ እኔን ከጠየቅከኝ አስከፊው ነገር ይህ ይመስለኛል፤ አንተስ አይመስልህም ?

በጦርነቱ በጣም ከተጎዱ ከተማዎች መካከል አታዬ አንዱ ይመስለኛል፡፡ ብዙ ተማሪዎች ቤታቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን አጥተዋል፡፡ ስለተከሰተው ጾታ ተኮር ጥቃትማ ማወቅ እንኳ አትፈልግም፣ እጅግ ልብ ይሰብራል! መንግስት ደግሞ ምንም እያደረገ አይደለም እድለኛ የሆኑት ብቻ አንድ ጊዜ ወደትምህርት ቤት ተመልሶ የመግባት እድል ነበራቸው፡፡ 

መንግስት እንዲያውቅ የምፈልገው አብዛኛዎቹ ጓደኞቻችን ወደትምህርት ቤት ተመልሰው አልመጡም፡፡ ሁሉም ተማሪ ወደ ክፍል ተመልሶ እንደሚመጣ ለማረጋገጥ ምን እያደረጋችሁ ነው? ሴት ልጆች በጦርነቱ ጊዜ ያጋጠማቸውን የስሜት መቃወስ መቋቋም እንዲችሉ ምን እያደረጋችሁ ነው? ወላጆችንስ ለመርዳት ምን እያደረጋችሁ ነው? — በጦርነቱ ጊዜ ሁሉንም ነገር ያጡትን — ልጆቻቸውን መልሳችሁ ወደ ትምህርት ቤት ትልካላችሁ ?

የምንጠይቀው ብዙ ነገር አይደለም፤ ለማህበረሰባችን ወደፊት መልሰን መስጠት እንድንችል እኛ የምንፈልገው መሠረታዊ እድል ማግኘት ብቻ ነው፡፡ 

የስነ ልቦና ባለሞያ መሆን እፈልጋለሁ ግን ሁል ጊዜ ሃሳቤን እቀይራለሁ፡፡ የልማት ሠራተኛ ሆኜ ማህበረሰቤን መርዳት እፈልጋለሁ፡፡ ቀበሌ እየሰራሁ ያለውን መጥፎ አስተዳደር ማስተካከልም እፈልጋለሁ፡፡ 


ሜሮን ሃይለሚካኤል፣14፣ ደብረሲና

ሜሮን ከደብረሲና የ14 ዓመት የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ነች፡፡ ስታድግ ዶክተር ወይም ኬሚስት መሆን ትፈልጋለች፡፡ 

ከጦርነቱ በፊት የተረጋጋ የትምህርት ህይወት ነበረን፡፡ እንደሚኒ ሚዲያ እና የሴቶች ክበብ ያሉ ብዙ ክበቦች አባል ነበረን፡፡ ፈተናዎች ቢኖሩብንም ትምህርት ማግኘት ይቻል ነበር፡፡ 

በህይወቴ ሙሉ ጦርነት በአይኔ አያለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም፡፡ ጦርነቱ ከተማችንን እየተጠጋ የመጣበት መንገድ እጅግ ድንገተኛ ነበር፡፡ በእኩለ ሌሌት ቅርባችን ወዳለ መንደር ሸሽተን ሄደን እዛም ለ3 ወራት ቆየን ፡፡ ውድመቱ እነደጠብቅነው መጥፎ አልነበረም እንደዛም ሆኖ የተወሰኑ ተማሪዎች ቤታቸውን አጥተዋል፡፡ 

ጦርነቱ በድጋሚ በማንኛውም ሰአት ሊነሳ ይችላል ይህም የሚያመጣው ስነልቦናዊ ተጽእኖ ከፍተኛ ነው፡፡ ትምህርታችን ላይ ማተኮር አንችልም ትተንም ሄደን ለወደፊት ህይወታችን የምንጓጓበት ምንም ምክንያት የለንም፡፡ ቀጥሎ ምን ሊከሰት እንደሚችል የማይታወቅበት ዘመን ላይ መኖርን እስኪ አስቡት፡፡ 

መንግስት ተማሪዎችን ከጦርነቱ ስነልቦናዊ ተጽእኖዎች ለመጠበቅ ምን እያደረገ እንዳለ ማወቅ እፈልጋለሁ፡፡ በድጋሚ እንደማይከሰትስ ለማረጋገጥ ምን እያደረጉ ነው?

በተጨማሪ የአካል ጉዳት ያለባቸው ሴት ልጆች በጦርነቱ ያልተመጣጠነ ተጽእኖ ደርሶባቸው ነበር፡፡ ሁላችንም ጦርነት ሴት ልጆች ላይ ያለውን ተጽእኖ እናውቃለን፡፡ መንግስት ይህን ለመፍታት ምን እያደረገ ነው?

ሴት ልጆች ማንኛውንም አይነት ጥቃት ሪፖርት ሲያደርጉ ፍትህ አያገኙም ይህ ደግሞ ወንጀለኛውን ያበረታታል፡፡ ፓሊሶች ደግሞ በጣም ያመነታሉ፡፡ ይህ ደግሞ ሴት ልጆች ሪፖርት እንዲያደርጉ አያበረታታም፤ ወንጀለኛው ደግሞ እያደረገ ያለውን እንዲቀጥልበት ያበረታታል፡፡ የፍትህ ስርዓቱን ለማስተካከል ያላችሁ አላማ ምንድን ነው?

flower.png
Meet the Author
Meet the Author
Ruth Yitbarek

(she/her) is a feminist advocate working with Malala Fund as a Network Coordinator for the Ethiopian chapter of the Education Champion Network.